bible
ra
🌐 Language
English
Español
Français
Deutsch
Português
Italiano
Nederlands
Русский
中文
日本語
한국어
العربية
Türkçe
Tiếng Việt
ไทย
Indonesia
All Languages
Home
/
Amharic
/
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
/
Haggai 1
Haggai 1
Amharic NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
Jump to:
Chapter 1
Chapter 2
Chapter 2 →
1
ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል ወደ ይሁዳ ገዥ ወደ ሰላትያል ልጅ ወደ ዘሩባቤልና ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኢዮሴዴቅ ልጅ ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲል መጣ፤
2
እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ፣ ‘ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ጊዜ ገና ነው’ ይላል።”
3
የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤
4
“ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?”
5
ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤
6
ብዙ ዘራችሁ፤ ነገር ግን ያጨዳችሁት ጥቂት ነው። በላችሁ፤ ግን አልጠገባችሁም። ጠጣችሁ፤ ግን አልረካችሁም። ለበሳችሁ፤ ግን አልሞቃችሁም። ደመወዝን ተቀበላችሁ፤ ግን በቀዳዳ ኰረጆ የማስቀመጥ ያህል ነው።”
7
እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤
8
ወደ ተራራ ውጡ፤ ዕንጨት አምጡ፤ ቤቱን ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፤ እከበርበታለሁም” ይላል እግዚአብሔር ።
9
ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ተስፋ አደረጋችሁ፤ ያገኛችሁት ግን ጥቂት ነው፤ ወደ ቤት ያስገባችሁትንም እኔ እፍ አልሁበት፤ ይህ የሆነው ለምን ይመስላችኋል? የእኔ ቤት ፈርሶ እያለ ሁላችሁም የራሳችሁን ቤት ለመሥራት ስለ ሮጣችሁ ነው፤
10
ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ሰማያት ጠል ከለከሉ፤ ምድርም ፍሬዋን ነሣች።
11
እኔም በዕርሻዎችና በተራሮች፣ በእህሉና በአዲሱ ወይን ጠጅ፣ በዘይቱና ምድር በምታፈራው ሁሉ፣ በሰውና በእንስሳ፣ በእጆቻችሁም ሥራ ላይ ድርቅ አመጣሁ።”
12
ከዚህ በኋላ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፣ ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፣ ከምርኮ የተረፉትም ሕዝብ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ፣ የነቢዩንም የሐጌን መልእክት ሰሙ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ልኮታልና። ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ።
13
ቀጥሎም የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሐጌ፣ ይህን የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ” ይላል እግዚአብሔር ።
14
ስለዚህ እግዚአብሔር የይሁዳን ገዥ፣ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፣ የሊቀ ካህናቱን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስና ከምርኮ የተረፈውን ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አነሣሣ፤ እነርሱም መጥተው የአምላካቸውን የእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት መሥራት ጀመሩ።
15
ይህ የሆነውም ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀን ነበር።
Jump to:
Chapter 1
Chapter 2
Chapter 2 →
All chapters:
1
2